Monday, January 14, 2013

ቅድሚያ ለሕፃናት ፕሮጀክት አንደኛ አመት የምስረታ በዓል


ውድ የ ቅድሚያ ለሕፃናት ስፖንሰሮች

ከሁሉ አስቀድሜ እንኳን ለፈረንጆች አዲስ አመት እንዲሁም ለፕሮጀክታችን አንደኛ አመት እግዚአብሔር በሰላም አደረሳችሁ እያልኩ በፕሮጀክቱ የበጎ አገልግሎት ሰራተኞችና በተረጆዎቹ ሕፃናት ስም መልካም ምኞቴን አስተላልፋለው።

በ2011 የመጀመሪያዎቹ ወራት ላይ በ4 ፈቃደኛ ስፖንሰሮች የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት አመቱ ከመጠናቀቁ በፊት ሌሎች 11 ስፖንሰሮችን በመጨመር ቁጥሩ ወደ 15 ማደግ ችሏል። እያንዳንዱ ስፖንሰር በስሩ አንድ ሕፃን ስለሚያግዝ፣ የተረጂዎቹ ሕፃናት ቁጥርም 15 ደርሷል ማለት ነው።

ይህ የስፖንሰሮች ቁጥር በያዝነው አዲስ የፈረንጆች አመት በግቢያ ላይ ወደ 17 ያደገ ሲሆን ይህን ቁጥር በቀጣዮቹ ወራት ውስጥ እያደገ እንደሚሄድ የሁላችንም ሙሉ እምት ነው። እርሶም በወር 25ዶላር በመክፈል ችግረኛ ልጆችን ስፖንሰር ሊያደርጉ የሚሹ ሌሎች ሰዎችን በማነጋገር የድርሻዎን ይወጡ ዘንድ ግብዣችንን እናቀርባለን።

ሕፃናቱ ከእርስዎ እና እንደእርስዎ ካሉ ሌሎች ስፖንሰሮቻቸው ባገኙት እገዛ ምክንያት ጤናቸው ተጠብቋል፣ በቂ ምግብ አግኝተዋል፣ ወደ ትምህርት ቤት ሄደዋል፣ እንዲሁም መንፈሳዊ እገዛ ለማግኘት በቅተዋል። የዚህ አወንታዊ ለውጥና እውነተኛ አምልኮ አካል በመሆንዎ እግዚአብሔር ይባርክዎ።

ይህን ልገሳዎን በዚህም አመት በመቀጠል እንዲሁም በጊዜው ወራዊ መዋጮውን ወደ አዲስ አበባ በመላክ ስፖንሰር የሚያደርጉትን የልጅዎን ሕይወት እንዲለውጡ እያሳሰብኩ እስካሁን ስላደረጉት የፍቅር ልገሳ የከበረ ምስጋና በፕሮጀክቱና በተረጂዎቹ ሕፃናት ስም አቀርባለው።   

ለድሀ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል፥ በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል። መጽሐፈ ምሳሌ 1917

አዳነው ዲሮ
የፕሮጀክቱ አስተባባሪ

No comments:

Post a Comment